ኽምራ ጤና ሳይንስ እና ቢዝነስ ኮሌጅ ከሰቆጣ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በመተባበርና በአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ የበለፀገውን EAIMS ዲጂታል ሲስተም ላይ ስልጠና አካሂዷል። ስልጠናው የመማር–ማስተማርና የአስተዳደር ሂደቶችን በዲጂታል መንገድ በብቃት ለመምራት የሚያስችሉ የንድፈ ሀሳብና የተግባር ልምምዶችን አካቷል።
ስልጠናውን በዘርፉ ልምድ ያለው አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ክብሮም መሰለ የሰጠ ሲሆን፣ የኮሌጁ ዲን፣ ምክትል ዲን፣ የዘርፍ ተጠሪዎች፣ መምህራንና የሪጅስትራር ባለሙያዎች በንቃት ተሳትፈዋል።
የEAIMS ሲስተም ዋና ጥቅሞች
- የመረጃ ተአማኒነትና ተጠያቂነት
የተማሪና የተቋም መረጃዎችን በአስተማማኝ ዲጂታል ስርዓት በመያዝ የመረጃ ጥራትን ያሻሽላል።
- የአሰራር ቅልጥፍና
የወረቀት ስራን በመቀነስ የተለያዩ የስራ ክፍሎችን በኔትወርክ ያገናኛል፤ መረጃን በፍጥነት ለማግኘትና ለውሳኔ አሰጣጥ ያመቻቻል።
- የስራ ጫናን መቀነስ
የመምህራንና የሪጅስትራር ባለሙያዎችን የዕለት ተዕለት ስራ በማቀላጠፍ ትኩረትን በትምህርት ጥራትና በተማሪ አገልግሎት ላይ ለማድረግ ያስችላል።
በአጠቃላይ ስልጠናው የኮሌጁን የዲጂታል አሰራር አቅም በማጠናከር የተማሪዎችን አገልግሎት፣ የመማር–ማስተማር ጥራትና የተቋሙን የአስተዳደር ቅልጥፍና ለማሻሻል የሚያግዝ ነው።
