Skip to content

የአብክመ ሥራና ሥልጠና ቢሮ የሰጠውን አቅጣጫ

የትምህርትና ስልጠና ጥራትን ይበልጥ ለማስጠበቅ፣ ብቁና በገበያ ላይ ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ለማፍራት እንዲቻል፤ የአብክመ ሥራና ሥልጠና ቢሮ የሰጠውን አቅጣጫ መነሻ በማድረግ የኽምራ ጤና ሳይንስ እና ቢዝነስ ኮሌጅ ሰፊ የስልጠና እና የውስጥ ጥራት ቁጥጥር ኮሚቴዎችን የማቋቋም መርሃ-ግብር በቀን 08/10/2018 ዓ.ም አካሂዷል።

በዕለቱ የኮሌጁ ከፍተኛ አመራሮች፣ የላይብረሪ ባለሙያዎች፣ አሰልጣኝ መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች በተገኙበት በሶስት ዋና ዋና አበይት ሰነዶች ላይ ያተኮረ ጥልቅ ስልጠና ተሰጥቷል።
1. በዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የተሰጡ ስልጠናዎች
ኮሌጁ ተደራሽነቱን ከመጨመር ባሻገር የሚሰጠው ትምህርት ዓለም አቀፍ መስፈርቱን የጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል በሚከተሉት ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይትና ስልጠና አድርጓል፦
የጥራት ማስጠበቅ (Quality Training)፦ በኮሌጁ የሚሰጡ የንድፈ-ሀሳብና የተግባር ስልጠናዎች የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ፣ የገበያውን ፍላጎት መሰረት ያደረጉና የተማሪዎችን ብቃት በሚያረጋግጥ መልኩ ስለሚመሩበት ስትራቴጂ ሰፊ ግንዛቤ ተፈጥሯል።
የዲጂታል ላይበራሪ ግንባታና አጠቃቀም፦ ተማሪዎችና መምህራን ወቅታዊና ዘመናዊ የማጣቀሻ መጽሐፍትን፣ የምርምር ስራዎችንና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በዲጂታል አማራጭ በቀላሉ የሚያገኙበትን አሰራር ለማዘመንና በስራ ላይ ለማዋል የሚያስችል ስልጠና በባለሙያዎች ተሰጥቷል።
የኢንስፔክሽን እና ሱፐርቪዥን (Inspection and Supervision) አሰራር፦ የመማር-ማስተማር ሂደቱ፣ የተቋሙ መመሪያዎችና የአደረጃጀት ስራዎች ስልታዊ በሆነ መንገድ የሚገመገሙበትና ክትትል የሚደረግበት መዋቅር ላይ ግልጽነት ተፈጥሯል።
2. የውስጥ ጥራት ማረጋገጫ ኮሚቴዎች መቋቋምና የወደፊት አቅጣጫ
የተሰጠው ስልጠና በተግባር መተርጎሙን ለማረጋገጥና ተቋማዊ ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ ኮሌጁ ሁለት ንዑሳን የውስጥ ጥራት ማረጋገጫ ኮሚቴዎችን በይፋ መርጦ አዋቅሯል። እነዚህም፦
የትምህርትና ስልጠና ክትትል ኮሚቴ፦ የመማር-ማስተማሩን ሂደት፣ የመምህራንን አፈጻጸምና የተማሪዎችን የብቃት ደረጃ በቅርበት የሚከታተልና የሚገመግም ኮሚቴ ነው።
የፊዚካል ፋሲሊቲ፣ መሰረተ-ልማት ግብዓት እና ዲጂታል ላይበራሪ ክትትል ኮሚቴ፦ የኮሌጁን የመማሪያ ክፍሎች፣ የቤተ-ሙከራ (Lab) ግብዓቶችን፣ አጠቃላይ የተቋሙን መሰረተ-ልማት እና የዲጂታል ላይበራሪውን ዝግጁነትና አገልግሎት ጥራት የሚቆጣጠር ኮሚቴ ነው።
የክትትል ስልት እና አቅጣጫ፦
ኮሌጁ ስራዎችን በዘፈቀደ ከመስራት ለመውጣት ዝርዝር የክትትልና ቁጥጥር ሰነድ (Checklist) ያዘጋጀ ሲሆን፣ ሁለቱም ኮሚቴዎች በተቀመጠው ቼክ ሊስት መሰረት በየኳርተሩ (በየሶስት ወሩ) ጥብቅ የውስጥ ሱፐርቪዥን በማድረግ ሪፖርት እንዲያቀርቡና የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ግልጽ አቅጣጫ ተቀምጧል።
ይህ የኮሌጁ ንቁ እንቅስቃሴ ኽምራ ኮሌጅ በጤና እና በቢዝነስ ዘርፍ ጥራቱን የጠበቀና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት ለመስጠት የጀመረውን ጉዞ ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን የግቢው አመራሮች ገልጸዋል።

Article topics